Home EBC ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ያስተላለፉት መልዕክት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ያስተላለፉት መልዕክት

by AddisDaily
25 comments

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ያስተላለፉት መልዕክት።

የመልዕክቱን ሙሉ ቃል ቀጥሎ ይቀርባል፡፡

ለመላ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱሰ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡

የገና በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሲል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በከብቶች በረት መወለዱን የምናስብበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ኃይል፣ ሥልጣን፣ ጦርነትና ጭቆና የለመዱት የዚያን ዘመን ሕዝቦች ግን ንጉሥ አድርገው የሚገምቱት በእግሩ ረግጦ፣ በእጁ ጨብጦ፣ በጦሩ ቀጥቅጦ፣ በሰይፉ ቆራርጦ የሚገዛቸውን ነበርና በትኅትና፣ በፍቅር፣ በይቅርታና በሰላም የመጣውን ጌታ ለመቀበል አልቻሉም፡፡

ክብርና ነጻነትን፣ ሰላምና ፍትሕን፣ ዕድገትና ብልጽግናን በተሳሳተ መንገድ ነበር ሲፈልጉት የነበሩት፡፡

በጦር አንደበትና በፈረስ ጉልበት ነበር ንጉሣቸውን የሚፈልጉት፡፡ የተሳሳተውን መንገድ እንደ ትክክል ስለቆጠሩትና ስለ ለመዱት፣ ትክክለኛው ንጉሥ በትክክለኛው መንገድ ሲመጣ እንግዳ ሆነባቸው፡፡

እንደ ሄሮድስ ያሉት ጦር ናፋቂዎች ለሰላም ጥሪው ሰይፍ መዘዙ፡፡

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ደግሞ ጥቅማችንን፣ ክብራችንንና ሥልጣናችንን እናጣለን ብለው ስለ ሰጉ ፍቅርን በጠብ፣ ይቅርታንም በብጥብጥ ሊያጠፉ ተነሱ፡፡

ከዚያ በፊት በሮማውያን ጭቆና ሲሰቃዩ የነበሩ የጎበዝ አለቆች፣ የመጣላቸውን ሰላም ማጣጣም አቅቷቸው ተሸነፈን በሚል ድርቅታ ደብቀውት የነበረውን ሰይፍና ጎመዳቸውን እንደገና ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡

የቤተ ልሔም ሕዝብም የክርስቶስ መወለድ በሕይወቱ የሚያመጣለትን ድኅነትና ለውጥ ሊገነዘበው ስላልቻለ በሩን ዘግቶ ተኛ፡፡

ድንግል ማርያምም ልጇን የምትወልድበት ሥፍራ አጣች፡፡ ጥቂት እረኞች ብቻ ነበሩ ነገሩ የገባቸውና፣ እየሆነ በነበረው ነገር በውል የተጠቀሙት፡፡ ወቅቱ እሥራኤላውያን የተከፋፈሉበት ወቅት ነበር፡፡

የሮም ደጋፊና ተቃዋሚ፤ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያንና ኤሴያውያን፤ አይሁዳዊና ሳምራዊ፣ ጸሐፍትና ቀራጮች፣ የሄሮድስና የጲላጦስ፣ ዐርበኛና ባንዳ በሚሉ የመከፋፈያ ጥጋጥጎች እስራኤላውያን እዚህ እና እዚያ ሆነው ይቆራቆሱ ነበር፡፡

ክርስቶስ የተወለደው በዚህ ጊዜ ነው፡፡

ሁሉም አልቀበለው ያሉት ነገሩን ከየጥቅማቸው አንጻር ብቻ ስላዩት ነው፡፡

እነርሱን ብቻ ካላከበረ፣ ካልጠቀመና ለእነርሱ ብቻ ካልመጣ ብለው እምቢ አሉት፡፡

የእነርሱ ብቻ እንጂ የሌሎችም ጭምር እንዲሆን አልፈለጉትም፡፡

ሰብአ ሰገል ከሩቅ ሀገር ዜናውን ሰምተው ሲመጡ፣ እዚያው ቤተ ልሔም ያሉት ግን ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብለው በግዴለሽነት ትተውት ነበር፡፡

የሮማውያንን ጭቆና፣ የጥንታዊት ሀገራቸውን መፈራረስ፣የታሪካቸውንና የማንነታቸውን መዳከም እያነሡ ይቆጫሉ፣ ይበሳጫሉ፡፡

ነገር ግን የጠፋውን ለመፈለግ፣ የወደቀውን ለማንሣት፣ የደከመውን ለማበርታትና የተሰበረውን ለመጠገን ከመጣው ከክርስቶስ ጋር ለመሆን ግን በፍጹም አልፈለጉም፡፡

ችግሩን ያውቁታል፤ መፍትሔውን ግን ትተውታል፡፡

ተባብረውና ተስማምተው የማያውቁት አይሁድና ሮማውያን እንኳን፣ ክርስቶስን ለመቃወም ሲሉ የጋራ ግንባር ፈጠሩ፡፡

የክርስቶስን ልደት ስናከብር እነዚህን ሁሉ ነገሮች አብረን ልናስባቸው ይገባል፡፡

የክርስቶስ ልደት የልዩነትን ግንብ ያፈረሰ፣ የጠብን ግድግዳ የናደ፣ የጥላቻን መጋረጃ የቀደደ፣ የተዋረዱትን ያከበረ፣ የተለያዩትን አንድ ያደረገ፣ የተበተኑትን የሰበሰበ ነው፡፡

የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ‹እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይለቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ እጅጉን ይልቃል› ተብሎ እንደ ተጻፈው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ይህ ስጦታ ታላቁ ስጦታ ነው፤ በመሆኑም ይህ በዓል የክርስትና አስተምህሮ መሠረት የሆነ ታላቅ በዓል ነው፡፡

አንድ ነገር ታላቅ ስጦታ ስለሆነ ብቻ ሁላችንንም አይጠቅምም፡፡ በቤተ ልሔም ከተማ ከነበሩት እንኳን ብዙዎቹ በክርስቶስ ልደት ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡

ልዩነቱ የተፈጠረው ስጦታውን በመቀበልና ባለመቀበል ነው፡፡

አብሮ በመሥራትና ባለመሥራት ነው፤ ዐውቆ በመጠቀምና ባለመጠቀም ነው፡፡

የቤተ ልሔም ሰዎች በከተማቸው የዓለምን ታሪክ የሚለውጥ ተአምር እየተሠራ መሆኑን አልተረዱም፡፡

እንኳን ታሪክ ሊሠሩ ታሪክ ሲሠራ ለማየትም አልፈቀዱም፡፡ ሌሎች ከሩቅ ሀገር ይህንን ታሪክ ለማየትና ለመስማት ሲመጡ ነው የደነገጡት፡፡ ሄሮድስም ራሱን ለመፈተሽ አልፈለገም፡፡

ሥልጣኑን በመሣሪያ ኃይል የሚያስጠብቅ መስሎት የቤተልሔም ሕጻናትን ነው ያስፈጀው፡፡
የሚገርመው ነገር የክርስቶስን መወለድ በቸልታ ያለፉት ግዴለሾቹ የቤተ ልሔም ሰዎች መከራው ግን አልቀረላቸውም፡፡

ሄሮድስ የጨረሰው የእነርሱን ልጆች ነው፡፡ መከራን በመጋፈጥ እንጂ በመተኛት ለማምለጥ አይቻልምና፡፡ ሊቃውንተ አይሁድም ዕውቀታቸውን እየጠቀሱ በመራቀቅ ጊዜውን ያለ ተሳትፎ አሳለፉት፡፡ ከተማሩት ሊቃውንት ይልቅ ያልተማሩት እረኞች ተጠቀሙ፡፡

ዛሬም እንኳን በታሪክ የምናስታውሰው እነርሱኑ ነው፡፡ የተናቁት የቤተልሔም ከብቶች ያደረጉትን አስተዋጽዖ ያህል በዳዊት ከተማ በመኖራቸው በታሪካቸው የሚመጻደቁት ቤተ ልሔማውያን አንዳች ለማድረግ አልቻሉም፡፡

የክርስቶስን መወለድ ስናስብ ሀገራችንንም እናስባት፡፡ በቤተ ልሔምና በዙሪያዋ የነበሩ ሁኔታዎች ዛሬም በሀገራችን አሉ፡፡

ቤተልሔማውያን በእጃቸው ያገኙትን ጸጋ መጠቀም አልቻሉም፤ በቅናት፣ በግዴለሽነት፣ በጥቅም ሽኩቻ፣ በየወገኑ በመከፋፈልና በሥልጣንጥም ተነክረው ዕድላቸውን አባከኑት፡፡

እኛም በዘመናችን ያገኘነውን ሀገራችንን የመለወጥ፣ የማሻሻል፣ የማሳደግና የማዘመን ዕድል እንዳናጣው እንደ ልባም ሰው ማሰብ አለብን፡፡

እንደ ቤተ ልሔማውያን በቅናት ተቃጥለን፣ በግዴለሽነት ተኝተን፣ በጥቅምና በሽኩቻ ተባልተን፣ በመከፋፈል ተበታትነን፣ በሥልጣን ጥም ሰክረን ያገኘነውን ዕድል ከእጃችን ላይ እንዳንጥለው የምናስብበት ጊዜ ላይ ነን፡፡

ክርስቶስ ሁሉን ነገር ትቶ በረት ላይ እንዲተኛ ያደረገው ለእኛ ለወገኖቹ ያለው ፍቅር ነው፡፡

የሚያሰልፈው የመላእክት ሠራዊት አጥቶ አይደለም፤ በመብረቅ ማጥፋት፣ በንፍር መምታት ተስኖትም አይደለም፡፡

ፍቅር ያድናል፣ ይቅርታ ይጠግናል ብሎ እንጂ፡፡ ወገናችንን በእውነት የምንወድ ከሆነ ሰላምን እንጂ ሰይፍን ለምን እናስቀድማለን? ፍቅርን እንጂ ጠብን ለምን እንሰብካለን? አንድነትን እንጂ መለያየትን ለምን እናመርታለን? ይቅርታን እንጂ ጥላቻን ለምን እንተክላለን? ይህ በዓልኮ ሰውና መላእክት፣ ፍጡርና ፈጣሪ፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሰማይና ምድር አንድ የሆኑበት በዓል ነው፡፡

መለያየትንና መጠፋፋትን እየዘራን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ‹ሰላም በምድር ይሁን› የተባለበት ነው፡፡ የጦርነትን ዘገር እየነቀነቅን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ እረኞችና ከብቶች መጠለያ ያጣውን ጌታ ያስጠለሉበት በዓል ነው፡፡

ታድያ ዛሬ ሂድ፣… ውጣ፣…. ልቀቅ፣…. እያልን የገዛ ወገናችንን እያሳደድን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ለወገን ጥቅም ሲሉ ራስን የመስጠት በዓል ነው፡፡

ለራሳችን ጥቅም ስንል ወገኖቻችንን እያጋደልን እንዴት ልናከብረው እንችላለን? ይህ በዓልኮ ሰውና መላእክት አንድ ሆነው የሰላም መዝሙር የዘመሩበት ድንቅ በአል ነው፡፡ ተለያይተን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰምን እንዴት ልናከብረው እንችላለን?

ሰብኣ ሰገል የተወለደውን ሕጻን ለማግኘት ከሄዱበት ዐውድ ብዙውን ነገር ቀይረው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን መጽሐፍ ይናገራል፡፡

እኒያ የጥበብ ሰዎች የሰላሙን ንጉሥ ካገኙት በኋላ በሌላ መንገድ – በሌላ ኃይለ ቃል እና በሌላ እምነት የመልስ ጉዟቸውን አድርገዋል፡፡

ሲሄዱ በሄሮድስ ቤተ መንግሥት በኩል ቢሆንም ሲመለሱ ግን ጎዳናቸውን ቀይረዋል፤ ሲመጡ ‹የአይሁድ ንጉሥ የት ነው?› እያሉ ቢፈልጉትም አግኝተውት ሲመለሱ ግን ‹የዓለማት ንጉሥ› ብለው ተናግረዋል፡፡ ‹ወዴት አለ?› ብለው እየፈለጉት መጥተው ነበር፡፡

አግኝተውት ሲመለሱ ግን‹ አገኘነው› ብለው ተደስተዋል፡፡ ከእነዚያ የጥበብ መንገደኞች መካከል ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንም ነበሩበት፡፡

እኛ የእነርሱ ልጆችም ዛሬ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ትኅትናን፣ አብሮነትን እና መከባበርን አስቀድመን መጀመር አለብን፡፡

እንዲያ ከሆነ የነገ ተነገ ወዲያ በዓሎቻችንን ‹ሰላማችን ወዴት አለ?› በሚል ጥያቄ ሳይሆን ‹ሰላማችንን አገኘነው‹ በሚል የማረጋገጫ ቃል እንደምናከብር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡

እኛም ከትዕቢት ይልቅ ትኅትናን ገንዘባችን ብናደርግ ወደ ጥላቻ እና ወደ መከፋፈል ከሚወስደው መንገድ ወጥተን በሌላ የፍቅር፣ የመደመር፣ የአብሮነት እና የመተማመን ጎዳና ወደ ከፍታችን እንደምንጓዝ እምነቴ የጸና ነው፡፡

‹የመጣው እና ይመጣ ዘንድ ያለው ለውጥ በሁላችንም ጥረት የመጣ ነው› ከሚለው የባለቤትነት ስሜት ጀምሮ ‹ለሁላችንም የሚበጅ ነው› እስከሚለው የመተማመን ጫፍ ድረስ ቅን መሆን ብንችል፤ ‹የእገሌ እና የእንቶኔ ለውጥ› ከሚል መጠቋቆም ተላቀን እና እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ለሁላችንም የምትበጅ ኢትዮጵያን እንደምንገነባ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡

ፈጣሪ ሀገራችንን የምናሳድግበትንና ራሳችንንም ለታላቅነት የምናበቃበትን ዕድል ሰጥቶናል፡፡

እንደ ቤተ ልሔም ሰዎች ስንዘናጋ፣ እንደ ሄሮድስ ሾተል ስንሞርድ፣ እንደ ሊቃውንተ አይሁድ በትንሽ በትልቁ ስንጨቃጨቅ፣ እንደ ዘመኑ ሰዎች ስንከፋፈል፣ እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሥልጣንና ጥቅም ቀረብን ብለን በኩርፊያ ስናምጽ፣ ዕድሉ እንዳያልፈን፡፡

እንደ እረኞችና እንደ ሰብአ ሰገል ዐውቀን እንጠቀምበት፡፡

የሚጠበቅብንን አድርገን የሚገባንን እናግኝ፡፡ ታሪክ ማለፉ ላይቀር ወቀሳና ከሰሳን ለትውልድ አናስተላልፍ፤ እኛ በሌሎች እንደተማርነው ሁሉ፣ ሌሎችም ነገ በእኛ መማራቸው አይቀርምና፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መልካም በዓል

ታኅሳስ 28፣ 2011 ዓ.ም

Source: EBC Ethiopian Broadcasting Corporation

You may also like

25 comments

Ethio Ethiopia January 6, 2019 - 10:39 am

ከ1966 አብዮት በኃላ የክርስቶስ እና የድንግል ማርያምን ስምን የሚጠራ ብቸኛ መሪ ዶ/ር አብይ አህመድ ነው ፡፡ ከመላው ቤተሰቦ ጋራ መልካም በዓል ይሁንዎ ፡፡

Tesfahun Abera January 6, 2019 - 10:53 am

This is the sound who follow JESUS!!

Kidanwa Mulugeta January 6, 2019 - 11:00 am

በጣም የምናከብርህ ውድ ጀግና ነህ ከቃላት በላይ ብዙ ትግስትን ካንተ ተምረናል ልብ ያለው ልብ ይበል ጥሩ መልክት ነው አብቹ መልካም በአል ከነ ቤተሰብዎ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን

Ewnet Yneger January 6, 2019 - 11:19 am

እኛም ወግ አየን እኮ ባካችሁ!
ይኼን ቀን ያላዩት አሳዘኑኝ::
ከተባረኩት ቤተሰቦችህ ጋር መልካም የገና በዓል ይሁንልህ የተወደድክ ጠቅላያችን :: ሺህ ዓመት ንገስ ::

u12a2u12e8u1231u1235 u1260u1242 u1290u12cd January 6, 2019 - 11:28 am

እግዚአብሔር ይጠብቅልን ምርጡ እና አንደኛው ጀግናው መሪዬ በዓላትን የጠበቀ እንኳን አደረሳችሁ እያለን በዓሉን የሚታሰብበትን የሚተነትን መሪ የሰጠን ፈጣሪ ይመስገን የምንም ጊዜ ምርጫዬ አብይዬ❤

Hiwot Shume January 6, 2019 - 11:33 am

full Of knowledge Dr Abiy He Knows Bible He Knows every thing we have Blessed Pm, Merry Christmas My Pm Thanks About ur wonderful message God Bless u Our Great Pm. & Merry Christmas to EBC.

Dagi Douglas January 6, 2019 - 11:36 am

What a messege… ለ ገባው አሁን ያለውን የሀገራችንን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳየበት መልእክት ነው።
ወዳጄ የ መፅሀፍ ቅዱስ ታሪክ ብቻ እያነበብክ እንዳይመስልህ

Tamirat Bekele January 6, 2019 - 11:45 am

Amen ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ አሊ ጌታ ዘመንህን ይባርከው አሁንም የጠላቶችህን ደጆች ጌታ አምላክ ያውርስህ መልካም የገና በዓል ለአንተና ለቤተሰቦችህ ይሁንላችሁ አሜን ስምዖን ” በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር።”(የሉቃስ ወንጌል 2:26) አንደሚለው የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር አንድ ቀን እጅህን የምጨብጥበት ቀን እንዲየመጣልኝ እለምነዎለው ደግሞም ይሆናል፡፡

Fasika Mulugeta January 6, 2019 - 11:46 am

ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።
ትንቢተ ኢሳይያስ 9 : 6
እንኳን አብሮ አደረስን!!!!

Abadi Girmay January 6, 2019 - 11:52 am

የ ክፍለዘመኑ ምርጥ ትምህርት እና ተግሳፅ ይገርማል ከሃይማኖት አባቶቻችን ማለትም ከአባ ጳዊሎስ አና ማትያስ አንደበት ያልተሞከረው ከአንድ ፖለቲከኛ ጣፋጭ ቁምነገር አዘል ትምህርት እናመሰግናለን መልካም ልደት ።

Zewdu Genemo January 6, 2019 - 11:56 am

አሜን። አንተን ለእኛ ለመላው ኢትዮጵያውን በረከት አድርጎ የሰጠን ሁሉን የሚችለው ኃያሉ አምላካችን ክብሩ ይስፋው! እግዚአብሔር አምላካችን ረዥም ዕድሜ ጤናና ሰላም ያብዛልህ። ፈጣሪ አንተንና የምታገለግለውን ህዝብ ይጠብቅ። እኛም ህዝብህ ሁል ጊዜ በጸሎታችን ከጎንህ ነን ብቻህን አይደለህም። አይዞህ በርታ ጽና እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነው!!!!

Ethiopian Moses January 6, 2019 - 12:01 pm

እንኩዋን አደረሰህ የምንወድህ መሪ ?የተወለደው ህፃን የአለም መድሃኒት የሆነው (ኢየሱስ ክርስቶስ ) ቤትህን እና አንተን ይባርክ !!! የጠላቶችህን ደጅ ውረስ ? መልካም የገና በአል ይሁንልህ ?

Aragaw Atinafu January 6, 2019 - 12:05 pm

long live for ethiopian hero

Tizibt Tirfu January 6, 2019 - 12:16 pm

እኔማ አንዳንዴ እንደው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ መጥቶ እንዳይሆን ኢትዮጲያን እየመራ ያለው እላለሁ፡፡ ስራህ ሁሉ እኮ የፈጣሪ አይነት ነው፡፡
መልካም በዓል ላንተም ከነቤተሰቦችህ፡፡

Gobeze Ayalew January 6, 2019 - 12:23 pm

ሰው ሲገባው ለተፈጠረለት አላማ ይኖራል ያኔ ደጋፊዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ተቃዋሚዎቹም ይበዛሉ ውጤታማነቱ ግን አያጠያይቅም እኛ ተመችቶናል እርስዎስ? እባክዎ አጠገብዎ ያለውን ጭቅጭቅ አይስሙ አርፈናል ገናም እናርፋለን

Ashebir Eshetu January 6, 2019 - 12:26 pm

ጠ/ሚሩ እንደ ፕሮቴስታንት ዘመዶቹ አንድ ጥቅስ እየመዘዘ ጥራዝ ነጠቅ ወሬ ሳይሆን ብልጥ ነውና የአበው ሊቃውንትን ትርጓሜና እውቀት እያጣቀሰ ምስጢርን ከሚስጢር እያስማማ ሲተነትን ሳይ ይህ ሰው ለምን ፕሮቴስታንት ሆነ እላለሁ???
እግዚአብሔር አለሙን ከፈጠረበት ጥበብ ይልቅ አለምን ያዳነበት ጥበብ የሚልቅ እንደሆነ ተፅፏል ሲል የተዋህዶ ሊቃውንት የሚተነትኑትን ትርጓሜ በጥንቃቄ እንዳነበበ እረዳለሁ!!!
ታዲያ ለምን ኢየሱስ ጌታ ነው ከሚል ጥቅስ በቀር ስብከት የሌለ ከሚያስመስሉት የፕሮቴስታንት ዕምነት ውስጥ አገኘነው??
በክርስቶስ መወለድ ሰባት ነገሮች አንድ ሆነዋል የሚለውን የሊቃውንት አስተምህሮ አስቀምጧል!
ከሰብአሰገል መካከል ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩ የሚነግሩንን የሊቃውንት ትምህርትም ጠቅሷል!!
ከ66 ውጪ ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ተረት እንጂ ወንጌል አይደለም ከሚሉት ወገኖች መሐል እንዴት አገኘነው????
የዚህን ሁሉ የወንጌል ምስጢር ተራቃ የምታራቅቀው ቤተክርስትያን ወንጌል አታውቅም አትሰብክም ጃጃቲያም ኮተታም ናት እያሉ 365 ቀናት ከሚሰድቧት ከሚከሷት ወገኖች እንዴት አገኘነው????
አሁን በጀመረው መንገድ ቀጥሎ ከነቤተሰቡ ኦርቶዶክስ እንዲሆን እየተመኘሁ….ላብቃ!!!
መልካም በአል!!!

u1270u123c u12d8u1265u1204u1228 u120du12f0u1273 January 6, 2019 - 12:46 pm

የተከበሩ መሪያችን እርሶ 1983ነበር ስልጣን መያዝ የነበረቦት ያው ስልጣኑ በተንኮለኞች እጅ ወደቀ ዛሬ ለደረስንበት ምስቅልቅል ህይወት ተዳረግን አሁንም እንደ ምክሮ እና እንደ እግዚአብሄር ፍቃድ ከኖርን እግዚአብሄር ስለ ኢትዮጵያ ይፈርዳል ሰላም ፍቅር ይነግሳል ሰላምና ፍቅር ካለ ሁሉ አለ ኢትዮጵያላይ 27 የተለቀቀው መርዝና ክፋት ሻጥር ከምድራችን ያጥፋልን መልካም የገና አል

Solomon Takele January 6, 2019 - 1:06 pm

Fetari amlak yirdah! Biruk yetebarek nehina hulum sirah indemisakalih emnete yetsena new!

Teklu Abebe January 6, 2019 - 1:13 pm

ለሁሉም መልስ አለው በቤተልሄም ግርግም የተውለደው ጌታ!!!እግዚአብሔር ይመስገን ተሰብኬም ተምሬም አሜን ብዮ ላንተም ለቤተሰቦችህም ለመላው ዓለም ክርስትያኖች በሙሉ እንኳን አብሮ አደረሰን!!!!!

Zerfe Negash January 6, 2019 - 1:13 pm

አንተን ሳያዩ ሳይሰሙህ ለሞቱት አዘንኩኝ አንተ ሰዉ ተመስለህ የመጣህ መልአክ ነህ ይሄ ቃል መችም የሰዉ ቃል አይደለም ሙሴን እና ህዝቡን ቀን በደመና አምድ ለሊት በእሳት አምድ የመራ የሚሄዱበትን መንገድ ያሳየ እግዝያብሄር ይምራህ ከሙሴ ጋር አፍ ለአፍ የተነጋገረ እግዝያብሄር በህልም በራእይ የናግርህ እንደዳዊት የልቤ ሰዉ ይበልህ እንደሰለሞን ጥበበኛ የአለምን ሁሉ እንቆቅልሽ ፈቺ ያርግህ አምላኩን የሚያዉቅ ህዝብ ይበረታልና አምላኬ ያበርታህ ታናናሽ ታላላቆች ሁሉ ልባቸዉን ጆሮዋቸዉን እጃቸዉን ይስጡህ በዘመንህኑ ሁሉ የተከናወነለት መሪ ተብለህ ታሪክ በአለም ይጻፍ የሚስተካከልህ አይገኝ መንግስትህ ይጽና አሜን አሜን አሜን

Abiyou Kebede January 6, 2019 - 1:23 pm

በምን ቃል እንምጀምር ግራ ገባኝ የአብይዬን የመልካም ምኞት መልእክት ኮሜንት ለማድረግ ። ከፍተኛውን መንፈሳዊ ስብዕናን የተላበሰ መልካም ምኞት ነው። እንኳን አብሮ አደረሰን ዶ/ር

Tiguh Mehari January 6, 2019 - 2:21 pm

ይሄን መልእክት ኮመንት ማድረግ እራሱ ይከብዳል ። ምን አይነት ሰምና ወርቅ የሆነ መልእክት ነው? በእውነት ሐገሬ መሪ አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ። በእውነት የኢትዮጵያ ህዝብ እረኛህውን አግኝቷል ፈጣሪውን ያመስግን ። የቤተክርስቲያንን ፀሎት እና ልመና ፤በየገዳሙ በበአት ተወስነው ያለቅሱ የነበሩትን የአባቶችን እምባ ፤የኢትዮጵያን ሕዝብ ጩኸትና ዋይታ ሰምቶ አንተን መሪ መካሪ ጠባቂ አድርጎ የሰጠን የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን። ላንተም ከመላው ቤተሰብህ ጋር መልካም በአል ይሁንልህ።

Abenezer Fikre January 6, 2019 - 2:45 pm

እንኳን አብሮ አደርሰን የሀገሬ ህዝቦቼ እና ውድ አብያችን መልካም ምክር ነው ኑሪልን አብያችን እንዋድሃለን ትንሺ ትልቅ ሳትል ሃይማኖት ሰትለይ ሁሉን አክባር ፍቅር የሆንክ ወንድማችን ነህ ሁሌም እንዋድሃለን።
We will together move our beloved country Forward

Hirut Temesgen January 6, 2019 - 3:24 pm

እውነት እግዚአብሔርን በጣም አመስግናለው ከሁሉ በፊት የጌታ ስም ይክበር ስለ አንተ ሌላ ምን እላለው በዚህ ክፉ ጊዜ እግዚአብሔር አንተን ለምድራችን መሪ አድርጎ ስለሰጠን ስሙ ይክበር እና በመቀጠል መልካም ምኞቴ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እስራኤላዊያን ነፃ ሊያወጣ በፈሪኦን ቤት ሙሴን አሳደገው እኔ እንደገባኝ ከሆነ በዚህ በኛም ዘመን አንተን ሸሽጎ ካስቀመጠበት አመጣልን የህዝቡን ጩኸት ሰምቶ እና ከሙሴ ጋር የነበረ ጌታ አንድም ቀን ከአተና ከስራክ አይለይ እንደ ሙሴ በታምር ከፍትህ ይቅደም በክፉ የሚያዩ ዓይኖች ይታወሩ በመቀጠል ለአንተና ለቤተሰብህ መልካም የልደት በዓል ይሁንላቹ

Kasahun Geremeskel January 6, 2019 - 4:15 pm

መሽረፈት/ር ዐቢይ አሕመድ/ እንዳንዴ እንደ ቄስ ኣንዳንዴ እንደ ወታደር ኣንዳንዴ እንደ ደላላ ኣንዳንዴ እነደ ጦንቋይ ኣንዳንዴ እንደ ኣስተማሪ ኣንዳንዴ እነደ ኣስተናጋጅ ኣንዳዴ እንደ ደራሲ ከሚያደርገው መንግስት ይሰውራችሁ

Comments are closed.